የአብነት ት/ቤት
አብነት ትምህርት ቤት
በአብነት ትምህርት ቤት ከፍተኛ ድካም ደክመው የተማሩ የቤተ ክርስቲያን
ምሁራን ዘመናዊ በሆነ መልክ የሚሰጠውን ትምህርት ሲማሩና በአብነት ትምህርት ቤት
ያገኙትን እውቀት እያገናዘቡ ሲያቀርቡት ማየት ትልቅ በረከት ነው። በዘመናዊው
ትምህርት ቤት ብቻ አልፈው በነገረ መለኮት ትምህርት ቤት በሚማሩ ሰዎች እና
በአብነት ትምህርት ቤቶች የአብነት ትምህርታቸውን ከቀሰሙ በኋላ በምስራቃውያንም
ይሁን በምዕራባውያን የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ገብተው በሚማሩ መካከል
ልዩነቶች አሉ። በአብነት ትምህርት ቤቶች ያለፈው ቤተ ክርስቲያንን ሁለገብ በሆነ
መንገድ የመረዳት፥ የደከመበትን ጥንታዊ ትምህርት በዘመናዊ አቀራረብ በልበ
ሙሉነት ለሌሎች የማስተዋወቅ ችሎታ፥ እናት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ
ክርስቲያን በእውነተኛ መልኳ እና ማንነቷ ለሌሎች የማስተዋወቅ ብቃት ይኖረዋል።
የዚህ ጽሑፍ ዋና ምክንያት መላከ ሰላም አባ ቃለ ጽድቅ መሉጌታ በቴዎሎጂ
ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ትምህርት ተምረው በመመረቃቸው ምክንያት ቀድሞ
የተማሩትን የአብነት ትምህርት ለማስታወስ ነው። ይህን ትልቅ የወንጌል ሐዋርያ አባት
በአብነት ትምህርት ቤቶች ያሳዩትን ጥረት እና ድካም በዘመናዊውም ስለደገሙት እሰይ
በጎ አደረጉ፣ እናትወት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ባደረጉት ጥረት በጣም ደስ
ብሎአታል፣ እርስዎንም እንኳን ደስ አለዎት ለማለት ነው። የዚህ ጽሑፍም ዓላማ ስለ
አብነት ትምህርት ቤቶች ምንነት፥ ስለሚሰጡት ትምህርቶች፥ ከዘመናዊው የትምህርት
ጋር በደረጃ ሲነጻጸሩ ምን እንደሚመስሉ፥ እና ዘመናዊው ተማሪ ከአብነት ተማሪ ጋር
ሲነጻጸር ምን እንደሚመስል በጭር ባጭሩ ለማሳየት ነው።
ብሂል፦የአብነት ትምህርት ቤት ማለት ከአባት የተገኘ፥ ከአበው የተወረሰ
ከጥንት የነበረ፥ የማንነት መገለጫ፥ በራስ ቋንቋ በራስ ፊደል፤ በራስ ሥራተ
ትምህርት የሚሰጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ ትምህርት የሚሰጥበት ትምህርት
ቤት ማለት ነው። የአንድን ሕዝብ የአንድን ሀገር ጥበብ እና ዕውቀት ለዚያ ሕዝብና
ለዚያች ሀገር ዜጎች የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ማለት ነው። ሥርዐተ-ትምህርቱ
አገር በቀል በሆኑ ብሔራውያን ሊቃውንት ተዘጋጅቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜም ዳብሯል።
የአብነት ትምህርት ቤት በልማድ «የቆሎ ትምህርት ቤት» በመባል በሕዝባችን ዘንድ
ይታወቃል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ «የቄስ ትምህርት ቤት» እንዲሁም አንዳንዶች
«የቤተ ክህነት ትምህርት ቤት» ይሉታል። የመጀመሪያው ልማዳዊ ስያሜ የተማሪዎቹን
አመጋገብና የችግር ኑሮ የሚገልጥ እንጅ የትምህርት ቤቱን ማንነትና ዓላማ የማያሳይ
በመሆኑ ተቀባይነት ያለው ስያሜ አይደለም። ሌሎቹ ስያሜዎች ግን የጥንታዊው
ትምህርት ባለቤቶች፣ የሥርዐተ ትምህርቱም ቀራጮች፣ መምህራኑም የቤተ ክርስቲያን
ሰዎች በመሆናቸው የሚመሳሰል ስያሜ ነው። የሃይማኖት አባቶች የጥንታዊ ሥልጣኔ
መነሻዎች፣ የዘመናዊ ትምህርትም መሠረቶች መሆናቸው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን
በሌሎችም ዓለማት ታሪክ የታወቀ ነው። ያም ሆነ ይህ ትክክለኛው ስያሜ «የአብነት
ትምህርት ቤት» ነው።
የአብነት ትምህርት ቤት የአንድን ሀገር ጥንታዊ ሥነ- ጥበብ፣ ሥነ-ፊደል፣
ሥነ-ዜማ፣ ሥነ-ባሕል፣ ሥነ-ሥርዐት፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ለዛ፣ ዝዬ፣ ወግና
ማዕርግ በልዩ ልዩ አቀራረብ፣ አገር በቀል በሆኑ ሊቃውንት፣ በአገር ቋንቋ፣ ባገር
ፊደል፣ አገር በቀል በሆነ የአስተምህሮ ስልት የሚያቀርብና የሚሰጥ የትምህርት ቤት
ነው።
የአብነት ትምህርት ዓለም አቀፋዊ ዕውቀትን የሚያንጸባርቅ፣ ዓለም አቀፍ
ይዘት ያላቸውን ትምህርቶች በሀገራዊ ደረጃ የሚያቀርብ ትምህርት ቤት ነው።
1
ትምህርቱም ለዜጎችም ለውጭ ሀገር ስዎችም ይሰጣል። በሀገር ውስጥ አእላፍ
ሊቃውንትን እንዲሁም ብዙ የውጭ ሀገር ሊቃውንት አፍርቷል።
በአብነት ትምህርት ቤት የሚሰጡ የትምህርት አይነቶች የአንድን ሕዝብ
ሁለንተናዊ የዕውቀት ዘርፎች ያካትታል። በሀገራችን የአብነት ትምህርት ቤቶች
ከሚሰጡት ትምህርቶች ዋና ዋናዎቹ ከዚህ የሚከተሉት ናቸው።
1,የፊደል እና የንባብ ትምህርት ቤት፦ በዚህ ትምህርት ቤት ፊደል፥ንባብ፥ ዳዊት
እና የመጀመሪያ ደረጃ የዜማ ትምህርት ይሰጣል። ይህም የንባብ እና የጽሑፍ መነሻ
የሚሆን መሠረተ-ትምህርት ነው። ይህም ትምህርት ቤት ፊደል ከማስቆጠር
ስለሚጀምር «የቁጥር፣ የንባብ ትምህርት ቤት» እየተባለም ይጠራል።
2,የቋንቋ ትምህርት ቤት፦ በቅኔ ቤት ግዕዝ ከነአገባቡ ይሰጣል፤ ግዕዙን ወደ አማርኛ
በመተርጎም ግዕዝን እና አማርኛን አስተባብረውና አዛምደው ያስተምራሉ። ይህም
ትምህርት ሥነ-ጽሑፍን፣ አገባብን፣ ንባብን፣ ምሳሌአዊ አነጋገርን እና የንግግር
ችሎታን ማሳወቅን ያካትታል።
3,የዜማ ቤት፦ በዜማ ቤት ከውዳሴ ማርያም ዜማ ጀምሮ በመስተጋብዑ በአርባዕቱ፣
በሠለስቱ፣ በጾመ-ድጓው፣ በድጓው፣ በዝማሬና መዋስዕቱ፣በአቋቋሙ፣ በቅዳሴው
እና በሌሎችም ከዜማ ጋር የተያያዙ ትምህርቶች ኢትዮጵያዊ ዜማ ለማደግ ችሏል።
የዚህም ትምህርት አባት ቅዱስ ያሬድ ነው። ይህም የደስታና የኀዘን ጊዜ ዜማዎችን፣
መዝሙርን፣ ማኅሌትን፣ ዘፈንን፤ ወየታን፣ ምሥጋናን፣ እንጉሩጉሮን እና ሌሎችንም
ከዜማ ጋር የተያያዙ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ የዜማ ቅኝቶች ሁሉ ያካትታል።
4,የቅኔ ቤት፦ በቅኔ ቤት የፈጠራ ችሎታ(creativity)፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን
የመረዳት ችሎታ(perspective and understanding)፣ የአዕምሮን ጥበብ
ሕግን ተከትሎና ቋንቋን መርጦ፣ አጋኖ ወይም አዋርዶ እንዲሁም መካከለኛ ደረጃ
ሰጥቶ ሁኔታዎችን የመግለጥ ችሎታ፣ ታሪክን እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ
የማቅረብ ችሎታ፣ ፍልስፍና፣ የአስተሳሰብ ችሎታ ትምህርት(critical
thinking) ይሰጥበታል። የቅኔን ባሕርይ እና የአሰጣጥ ስልት ልብ ብሎ ላስተዋለው
ከላይ የዘረዘርኩአቸውንና ሌሎችንም ጥበቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያጠቃልላል።
ከዚህ በተጨማሪ ቅኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገዶች ያሉት በመሆኑ እንደየ መንገዱ
ልዩ ልዩ የአቀራረብ ስልትን እና የቋንቋን አገባባዊ መዋቅርን እና ቋንቋዊ ሙያን
ለመማር ያስችላል።
5,ትርጓሜ ቤት፦ በዚህ ትምህርት ቤት የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ይሰጥበታል።
ይህም ትምህርት ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ብሔራዊ በሆነ መልኩ የቀረበ
የኢትዮጵያን ሊቃውንት ዕውቀት ደረጃና ጥንታዊ አስተምህሮ የሚያስረዳ የአብነት
ትምህርት ቤት ነው። ይህ ትምህርት ቤት በሀገራችን ጥንታዊ ሥርዐተ ትምህርት
ከፍተኛው የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ነው።
6,የቁጥር ትምህርት ቤት፦ የሂሣብ ትምህርት በረቀቀ ሁኔታ ይሰጥበት የነበር የአብነት
ትምህርት ቤት ነው። ይህ ትምህርት ቤት የስነ ከዋክብት ትምህርት፣ ሚጠተ
ብርሃናት(የብርሃናት ምልልስ)፣ የዘመን አቆጣጠር ትምህርት የሚሰጥበት ትምህርት
ቤት ነው። ዛሬ ግን ከሌሎች የአብነት ትምህርት ቤቶች ይልቅ ይህ የአብነት ትምህርት
ቤት ተዳክሞ መምህራኑ ጠፍተዋል ጥበቡም ደብዝዟል። ትምህርቱን ያውቁት የነበሩት
የጥንት ሊቃውንትም አልቀዋል። ርዝራዡ ሳይጠፋ ይህን ጊዜ በዚህ ሙያ ዙሪያ
ዕውቀት ያላቸውን ሊቃውንት በማሰባሰብ እና ጥንታውያን የቁጥር መጻሕፍትን
በመመርመር ትንሣኤ እንዲያገኝ ካልተደረገ ወደ ትውልድ ሳያልፍ ትልቁ ጥበብ
መቅረቱ ነው። ይህም ለሀገራችን እና ዕውቀትን ጥበብን ለሚራቡ ሁሉ ትልቅ ጉዳት
ነው።
ከላይ በተዘረዘሩት የአብነት ትምህርት ቤቶች የኢትዮጵያውያን ጥንታዊ
አስተምህሮ፥ ሃይማኖት፥ ትውፊት፥ ስርዓት፥ ወግ፥ ልማድ፥ ቋንቋ፥ ሥነ-ጽሑፍ፥
ዜማ፥ ትርጓሜ መጻሕፍት፥ ሥርዐተ ማኅሌት፥ ክብርና ታሪክ ከትውልድ ወደ
2
ትውልድ መተላለፍ ችለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመላ
ሀገሪቱ በሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ይልቁንም በጎንደር፥ በጎጃም፥ በሰሜን
ሽዋ፥ በትግራይ፥ በዋድላ፥ በደላንታ እና በላስታ(በወሎ)በሚገኙት የአብነት ትምህርት
ቤቶች ዕውቀትን የሚራቡትን በመመገብ በኢትዮጵያ አብነትነት ያለው፣ አንቱ
የሚያስኝ ትምህርት እንዲስፋፋ በማድረግ ታላቅ በረከትን ለትውልዱ አበርክታለች።
ይልቁንም ጎጃምና ጎንደር እስከ ዛሬ ድረስ የሀገሪቱ ዋና የአብነት ትምህርት ማዕከላት
ናቸው።ይህንን በተመለክተ ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ የሚባሉ
ሊቅ«መርሐ ልቡና» በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል።
«ከኢትዮጵያም ጎጃም እና ስመ-ጥሩውን ጎንደርን በጣም ማመስገን ይገባናል።
አይሮፓውያን የሊቃውንትን ትምህርት ቤት ዩኒሸርሲቲ እንደ ሚሉት፣ ጎንደርና ጎጃምም
እንደዚሁ በኢትዮጵያ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዩኒሸርሲቲ መሆናቸው የታወቀ ነው። ጎንደር
በሐዲስ መጽሐፍና በሊቃውንት መጽሐፍ በዜማ ባሕልና ሥርዐት በማናቸውም በኩል አብነት
መባል ይገባዋል። ጎጃምም እንደዚሁ በመጻሕፍተ ብሉያትና በቅኔ በጥንታዊ ባሕልና ታሪክ
በኩል ምስክር መባል አለበት። ስለዚህም ሁለቱ ሀገሮች ዩንሽርሲቲ መባል ይገባቸዋል።
ከሁሉም ይልቅ የሚያስደንቅ እነዚህ ሁለቱ ሀገሮች ከሁሉም አውራጃዎች የትምህርትን ማዕድ
ለመሳተፍ የመጡትን በብዙ ሽህ የሚቆጠሩትን ተማሪዎች አስፈላጊውን ትምህርት ጨርሰው
እስኪመለሱ ድረስ እስከ ሃያ ወይም እስከ ሰላሳ ዘመን ድረስ ቢቀመጡ፣ የሀገሩ ተወላጆች
ምዕመናን ምግባቸውን ያለማቋረጥ ስለሚመግቧቸው እና፣ለመምህራንም ዋጋ መክፈል
ስለሌለባቸው ምኞቱን ከፍጻሜ የማያደርስ ተማሪ አይገኝም። ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ሀገሮች
መንደሩን እየከፈሉ ስለሚሰጡአቸው ተማሪዎች ያለ ሀሳብ ትምህርታቸውን ለመቀጠል
በምግብና በማናቸውም ረገድ አሳብ የለባቸውም። ስለዚህ በተማሪዎች አኳኋዋን ጎጃምና
ጎንደር፣ ዋድላና ላስታ የእናት የአባት ቤት መባል ይገባቸዋል» (ገጽ 4)
የአብነት ትምህርት ቤቶች ለቤተ መንግሥት እና ለኅብረተሰቡ ያበረከቱት አገልግሎት
በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠውን ትምህርት የተማሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት
ክርስቲያኖች ነበሩ። አናዳንዶቹም ካህናት ነበሩ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአብራኳ
የተከፈሉት ነገሥታት ሕዝባቸውን የሚመሩበትን ሕግና ጥበብ ታስተምር ነበር።
በመሆኑም የሕግ ትምህርት በመደበኛነት ይሰጥ ነበር። መምህራንም የነገዎቹን የሀገር
መሪዎች የዛሬዎቹን ደቀ መዛሙርቶቻቸውን በሃይማኖት እና በፈሪሃ እግዚአብሔር፣
በሕግና በሥርዐት እንዲያስዳድሩ ያሰለጥኑአቸው ነበር። ለምሳሌ አባ ኢየሱስ ሞዐ
የአፄ ይኩኖ አምላክ መምህር ነበሩ። ሌሎችም በዛጉዬ ዘመነ መንግሥት የነበሩ
ነገሥታት ላሊበላን ጨምሮ ካህናት ነበሩ፤ ባክሱም ዘመነ መንግሥትም የነበሩት እነ
አጤ ገብረ መስቀል ፍጹም መንፈሳውያን ነበሩ። በጎንደሮች ዘመነ መንግሥትም እነ
አጤ ኢያሱ አድያም ሰገድ ካህናት ነበሩ። የቅኔ ዘራፊዎች ሊቃውንትም የነበሩ
ነገሥታት እንደነበሩ ታሪካችን ይመሰክራል(ለምሳሌ አፄ በእደ ማርያም አፄ በካፋ)።
የቤተ መንግሥቱ የፍርድ ቤት ዳኞች የነበሩትም የቤተ ክርስቲያኒቱ የሕግና
የስርዓት ሊቃውንት የነበሩ ናቸው። በዚህ ትምህርት ቤት ሃይማኖት፥ ትውፊት፥
ስርዐት፥ ወግ፥ ልማድ፥ ቋንቋ፥ ሥነ-ጽሑፍ፥ዜማ፥ ትርጓሜ መጻሕፍት፥ ሥርዐተ
ማኅሌት፥ ክብርና ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ ችለዋል። በአፍሪካ ብቸኛ
የሆነው የግዕዝ ፊደል ከነሙሉ ጥበቡ የተረፈው በዚሁ ትምህርት ቤት ነው። አሁን
ከዚህ ላይ ልገልጸው ጊዜና ቦታ ባይፈቅድልኝም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአብነት
ትምህርት ቤቶች አስተዋጽኦ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያ መንግሥት ሁለገብና
ብሔራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑ የታወቀ ነው። ከዚህ ቀጥሎ በእነዚህ የአብነት
ትምህርት ቤቶች የሚሰጡትን ዋና ዋና ትምህርቶች ደረጃ እየሰጠን እናቀርባለን።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት – ፊደል፣ አቡጊዳ፣ መልእክተ ዮሐንስ፣ የአነባበብ ስልት
ትምህርት ንባብ (ማጋዝ፣ ውርድ ንባብ፣ ቁም ንባብ) ቀን ቀን ሲሰጡ ሌሊት ሌሊት
ደግሞ የቃል ትምህርት ይሰጣል። ይሄውም የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣
አንቀጸ ብርሃን፣ መልክዓ ማርያም፣ መልክዓ ኢየሱስ፣ እና ውዳሴ ማርያም ዜማ
ናቸው። ከዚህ በኋላ ቀን ቀን ንባቡን አቀላጥፎ ካነበበ በኋላ ዳዊት ይጀምራል።
ዳዊቱን ተምሮ ሲጨርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ሁለተኛ ደረጃ
3
ትምህርት ቤትም እንዳለፈ ይቆጠራል። ከዚያ በኋላ ትምህርቱን በቀን ብቻ ሳይሆን
በሌሊትም አጠናክሮ ይቀጥላል። የሌሊቱ ትምህርት የቃል ትምህርት ሲሆን በቃል
የሚጠና፣ በአእምሮ የሚወሰን ሲሆን በቀን የሚሰጠው ትምህርት ደግሞ በመጽሐፍ
የሚጠና ነው። ስለዚህ በዚህ ጸሐፊ አስተያየት ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጋራ
ሊነጻጸር የሚችለው ሌሊት የሚሰጠው ከቃል ትምህርት፣ ከዘወትር ጸሎት እስከ
መልክዓ ኢየሱስ ያለው በቀን ከሚሰጠው ትምህርት ደግሞ ፊደልን አቡጊዳን (የፊደል
አካል ነው) መልእክተ ዮሐንስን ተምሮ ከዚያ በኋላ የግዕዝ ንባብ በሚማርበት
መጽሐፍ ግእዝ ውርድ ንባብ ቁም ንባብ አውቆ ዳዊት ተምሮ ሲያጠናቅቅ ነው።
ንባብ- ይህ ደግሞ ተማሪው መምህሩ ንባብ በሚያስተምርበት የግዕዝ መጽሐፍ
መጀመሪያ በግዕዝ የአነባበብ ስልት፣ ሁለተኛ በውርድ ንባብ የአነባበብ ስልት (ተነሺና
ተጣይን ለመለየት በጣም ጠቃሚ የሆነ የአስተምሮ ስልት ነው)፣ ከዚያም
በመጨረሻም በቁም ንባብ (መደበኛው የግዕዝ መጻሕፍት የሚነበቡበት የአነባበብ ስልት
ቁም ንባብ ይባላል) ንባብ ይማራል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ተማሪው ዳዊት ይማራል።
ዳዊትም የሚማረው በሁለት የአነባበብ ስልት ነው። አንደኛ በዕዝል ሁለተኛ በቁም
ንባብ ይማረዋል። በዚህ መልኩ ከፊደል እስከ ዳዊት አጠናቆ የተማረ ተማሪ ዳዊት
ሲደግም ማለት ዳዊት ተምሮ ሲጨርስ (አንድ መቶ ሃምሳውን መዝሙረ ዳዊት፤
ነቢያትን እና መኃልየ ሰሎሞንን ያጠቃልላል) በከፍተኛ ሁኔታ ይደሰታል። አንዳንድ
ቤተ ሰቦች ለልጆቻቸው አስተማሪዎች ለዚህ ደረጃ ስላደረሱላቸው የደስታ ስጦታም
ያበረክታሉ። ይህ ተማሪ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ተማሪን ይመስላል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት – በቃል ትምህርት በኩል ውዳሴ ማርያም ዜማ፣
መስተጋብዕ፣ ግብረ ዲቁና፣ ሰዓታት፣ አርባዕት ተምሮ ለዲቁና እና ለቅስና
የሚያበቃውን የቃል ትምህርት ሲጨርስ ከፍተኛ ሁለተኛ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ተማሪን
ይመስላል። ለሥራ የሚያበቃ ሁለገብ የሆነ እውቀት ገብይቶአልና። በቀኑ ትምህርት
በኩል ደግሞ ቅኔ ተቀኝቶ ለራሱ ያክል ሲያውቅ ሩቅና ቅርብ፣ አንድና ብዙ፣ ወንድና
ሴት ለይቶ የመጻሕፍትን ሐሣብ ተረድቶ ሌሎችን ለማስረዳት ከሚያስችል ደረጃ
ሲደርስ ከአንድ ማሠልጠኛ ገብቶ ለሥራ የሚያበቃ ሥልጠና አግኝቶ መረጃ ይዞ የወጣ
ተማሪን ይመስላል። ይህ ደረጃ ከመጀመሪያ ድግሪ ጋርም ሊነጻጸር ይችላል። እንደ
እውነቱ ከሆነ በድካም ደረጃ ከፍተኛ ድካም ነው ተማሪው የሚደክመው። ነገር ግን
ዘመናዊው ትምህርት ልዩ ልዩ የትምህርት ዓይነቶችን ያካተተና በተቀላጠፈ መልኩ
የሚሰጥ በመሆኑ በእውቀት ደረጃው ሊመሳሰል ይችላል።
ዲግሪ – አንድ ሰው ከዚህ ሁሉ ጋር አቋቋም ለራሱ አውቆና ራሱን ችሎ ለመቆም
የሚያስችል እውቀት ካለው፥ ዜማና ቅኔም ለራሱ ያክል በሚገባ ከወቀ ከማስትሬት
ዲግሪ ጋር እኩያ ሊሆን ይችላል።
ፒ ኤች ዲ – በቤተ ክርስቲያን ብዙ የእውቀት ዘርፎች አሉ። እነርሱም ከዜማ ጋራ
የተያያዙ ከቅኔ ጋር የተያያዙ እንዲሁም ከመጻሕፍት ትርጓሜ ጋራ የተያያዙ ናቸው።
1) በዜማ በኩል ለምሳሌ አንድ ሰው የድጓ መምህር፣ የአቋቋም መምህር፣ የዝማሬ
መዋስዕት መምህር፣ የቅዳሴ መምህር ሆኖ በመምህርነት ቢመረቅ
2) በቅኔ በኩል ቅኔ ከእነ አገባቡ አውቆ ልዩ ልዩ የቅኔ መንገዶችን ቀጽሎ
በመምህርነት ቢመረቅ
3) በትርጓሜ መጻሕፍት በኩል ከአራቱ ጉባኤያት በአንዱ (በመጻሕፍተ ሐዲሳት
ትርጓሜ ፣ በሊቃውንት ትርጓሜ መጻሕፍት፣ በብሉያት ትርጓሜ፣ በመጻሕፍተ
መነኮሳት ትርጓሜ) የተመረቁ መምህራን የሆኑ በተወሰነ ሙያ ላይ የተለየ ጥናት
ያደረጉ ባለሙያዎች ስለሆኑ ፒ,ኤች,ዲ ካለው አንድ ዘመናዊ ምሁር ጋራ ድካማቸው
እና እውቀታቸው ሊነጻጸር ይችላል። በጠቅላላ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እውቀት
በባለሙያዎች በሚገባ ተጠንቶ ቢመዛዘን ዋጋው ከላይ ከተጠቀሰው ግምገማ ቢሻል
እንጂ አያንስም ብዬ እገምታለሁ።









