የሰንበት ት/ቤት
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት – በቃል ትምህርት በኩል ውዳሴ ማርያም ዜማ፣
መስተጋብዕ፣ ግብረ ዲቁና፣ ሰዓታት፣ አርባዕት ተምሮ ለዲቁና እና ለቅስና
የሚያበቃውን የቃል ትምህርት ሲጨርስ ከፍተኛ ሁለተኛ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ተማሪን
ይመስላል። ለሥራ የሚያበቃ ሁለገብ የሆነ እውቀት ገብይቶአልና። በቀኑ ትምህርት
በኩል ደግሞ ቅኔ ተቀኝቶ ለራሱ ያክል ሲያውቅ ሩቅና ቅርብ፣ አንድና ብዙ፣ ወንድና
ሴት ለይቶ የመጻሕፍትን ሐሣብ ተረድቶ ሌሎችን ለማስረዳት ከሚያስችል ደረጃ
ሲደርስ ከአንድ ማሠልጠኛ ገብቶ ለሥራ የሚያበቃ ሥልጠና አግኝቶ መረጃ ይዞ የወጣ
ተማሪን ይመስላል። ይህ ደረጃ ከመጀመሪያ ድግሪ ጋርም ሊነጻጸር ይችላል። እንደ
እውነቱ ከሆነ በድካም ደረጃ ከፍተኛ ድካም ነው ተማሪው የሚደክመው። ነገር ግን
ዘመናዊው ትምህርት ልዩ ልዩ የትምህርት ዓይነቶችን ያካተተና በተቀላጠፈ መልኩ
የሚሰጥ በመሆኑ በእውቀት ደረጃው ሊመሳሰል ይችላል።
ዲግሪ – አንድ ሰው ከዚህ ሁሉ ጋር አቋቋም ለራሱ አውቆና ራሱን ችሎ ለመቆም
የሚያስችል እውቀት ካለው፥ ዜማና ቅኔም ለራሱ ያክል በሚገባ ከወቀ ከማስትሬት
ዲግሪ ጋር እኩያ ሊሆን ይችላል።
ፒ ኤች ዲ – በቤተ ክርስቲያን ብዙ የእውቀት ዘርፎች አሉ። እነርሱም ከዜማ ጋራ
የተያያዙ ከቅኔ ጋር የተያያዙ እንዲሁም ከመጻሕፍት ትርጓሜ ጋራ የተያያዙ ናቸው።
1) በዜማ በኩል ለምሳሌ አንድ ሰው የድጓ መምህር፣ የአቋቋም መምህር፣ የዝማሬ
መዋስዕት መምህር፣ የቅዳሴ መምህር ሆኖ በመምህርነት ቢመረቅ
2) በቅኔ በኩል ቅኔ ከእነ አገባቡ አውቆ ልዩ ልዩ የቅኔ መንገዶችን ቀጽሎ
በመምህርነት ቢመረቅ
3) በትርጓሜ መጻሕፍት በኩል ከአራቱ ጉባኤያት በአንዱ (በመጻሕፍተ ሐዲሳት
ትርጓሜ ፣ በሊቃውንት ትርጓሜ መጻሕፍት፣ በብሉያት ትርጓሜ፣ በመጻሕፍተ
መነኮሳት ትርጓሜ) የተመረቁ መምህራን የሆኑ በተወሰነ ሙያ ላይ የተለየ ጥናት
ያደረጉ ባለሙያዎች ስለሆኑ ፒ,ኤች,ዲ ካለው አንድ ዘመናዊ ምሁር ጋራ ድካማቸው
እና እውቀታቸው ሊነጻጸር ይችላል። በጠቅላላ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እውቀት
በባለሙያዎች በሚገባ ተጠንቶ ቢመዛዘን ዋጋው ከላይ ከተጠቀሰው ግምገማ ቢሻል
እንጂ አያንስም ብዬ እገምታለሁ።









